ያኔ ልጅ እያለሁ በህይወት የደረስኩባቸው አያቶቻችን ሲያወሩትና ሲሰሩት እሰማውና አየው ከነበሩት የዕለት ከዕለት ውሏቸው የማስታውሰው፣ ወገኖቻችን በእርሻ፣ በቤተክህነት አገልግሎት፣ በንግድና ያን ጊዜ ቤተክህነት ትሰጠው ከነበረው የቀለም ትምህርት ጋር በወቅቱ ይሰጥ የነበረው ዘመናዊ ትምህርት የተማሩት ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑት ደግሞ በሀገር አስተዳደር ውስጥ ይሰሩ እንደነበር ነው።
ከእነዚህ አያቶቻችን የተበራከተው ትውልድ በየፊናው ተሰማርቶ መስራቾቹን ሙያወች ሳይለቁ በግብርናው፣ በቤተ ክህነት አገልግሎትና በንግዱ አለም ተሰማርተው የሚገኙ ቤተሰቦች ያሉንን ያህል፣ ከጊዜ ጋር እየተለወጠና እየተሻሻለ የመጣውን የሀገር ውስጥና የውጭ ትምህርት በመማር፣ በህክምና፣ በህግ፣ በአስተዳደር፣ በምህንድስና፣ በአየር በባህርና በየብስ የምድር ትራንስፖርት፣ በማስተማር፣ በህትመት፣ በሞዴልነትና በትወና፣ በቤት እመቤትነት፣ በውትድርና፣ በግንባታና በሌሎች የእጅ ሙያወችና የተለያዩ የህዝብ አገልግሎትና የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው በሀገር ውስጥ (በኢትዮጵያና) ከሀገር ውጭ ይኖራሉ። አብዛኞቹ ወልደው ተዋልደው ተበራክተዋል። በዚህ ህትመት ያሉበትን እና የሚሰሩትን ስራ ባይጠቀስም፣ የተቻለውን ያህል ለመንደርደሪያ ያህል የሚሆን የስም ዝርዝራቸው ተካቷል። በዝርዝሩ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች ህይወታቸው ያለፈውና አብረውን የሌሉ በዚሁ ህትመት
ተካተዋል።
ይህ ህትመት በህይወት ያሉትን ልጆችና የልጅ ልጆች ያገናኛል ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ ወቅት ወይም በሌላ ሁሉም ሰው የሚጠይቀውን የእኔ ማን ነኝ ጥያቄ በሙሉ ባይመልስም ትንሽ ፍንጭ ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ። ይህ ሀሳብ ወደፊት ተጠናክሮ ከቀጠለ ቴክኒዎሎጂውም እገዛ ስለሚያደርግ በበለጠ ተደራሽነት የሚኖረውና ቢቻል በአካል ካልሆነም በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ያገናኛል ። ዛሬ በትንሹ የወጣው ወደፊት ፎቶ ግራፎችና ሌሎች ዝርዝሮች ሲጨማመሩ የህትመቱ ብዛትና ጥራት ከማደጉ ባሻገር፣ ማን የት አለ ብሎ የማወቅን ፍላጎትም ከፍ ያደርጋል። ዛሬ በአማርኛ ብቻ የታተመው በሌሎችም ቋንቋወች እንዲታተም ይሆናል። በድጋሚ ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክትና ተባብረን ሀሳቡን አበልፅገን ለትውልድ የሚተላለፍ ሥራ እንድንሰራ በትህትና እየጠየቅሁ የህትመቱን ሥራ ለመሥራት ከወዲሁ ቃል
እገባለሁ።
አመሰግናለሁ